TARIKAWI BEDEL BE ETHIOPIA MUSLIM LAY

ﺑﺴﻢﷲﺍﻟﺮﺣﻤﻦﺍﻟﺮﺣﻴﻢ 
ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው የደረሰባቸውን ሐይማኖታዊ የመብት ጥሰት በመቃወም ስርዓቱን በጠበቀ መንገድ ጥያቄያቸውን በድምጻቸው ለመረጡት መንግስት ቢያሰሙትም ምላሹ 20 ዓመታትን በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ካሳለፈ አገዛዝ ይቅርና 20 ቀናት በዲሞክራሲ ስርዓት ከቆየ አገዛዝ የማይጠበቅ መሆኑ ልብን የሚያደማ ነው፡፡ 
እንደ ዜጋ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ተጥሶ ስናየው፣ መብታችንን እንደ የእግር ኳስ ከወዲህ ወዲያ እያላጉ እንቅርቅቦሽ ሲጫወቱበት ጉዳቱ ሲያመን ጊዜ ህግ እና ሥርዓት ባለበት አገር ህግና ሥርዓትን ጠብቀን በአንድ መድረክ ተሰብስበን ስናበቃ ጥያቄያችን እንዴት ሊሰማ እንደሚችል ተወያይተን ወኪሎቻችንን ህጉ በሚያዘው ቅደም ተከተል መርጠን፣ጥያቄዎቻችንን ለአረዳድም ሆነ ለምላሽ በማያዳግት መልኩ እጥር ምጥን አድርገን ለመንግስት አቀረብን፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን ተጉዘን ሰባት ወራትን አስቆጠርን፡፡ ይህ ሂደታችን ለራሳችን እስኪገርመን ድረስ አስተማሪነቱ ድንበር ተሻጋሪ ሆኖ አገኘነው፡፡ ይህ ሂደታችን ራሱ የኢሕአዴግ የስራ አስፈፃሚ ጉባዔንም ጭምር እንዳነጋገረ የምናውቀው እውነታ ነው፡፡ 
ጥያቄዎቻችን ፍፁም ሐይማኖታዊ እና ሐይማኖታዊ ናቸው፡፡ በምን ቋንቋ ይሆን እነኚህ ሦስት ጥያቄዎቻችን ሐይማኖታዊ ብቻ ከመሆን ሊዘሉ የሚችሉት? ጥያቄዎቹ እኮ!
1. የመጅሊስ አመራሮች አይወክሉንም፣ምርጫ ይደረግ፣
2. የአሕባሽ የግዳጅ አስተምህሮት ይቁም እና
3. አወሊያ ከህዝብ በተመረጠ ገለልተኛ የቦርድ አመራር ይተዳደር የሚሉ ናቸው፡፡
እነኚህን ጥያቄዎች መመለስ የአንድ ቀን እና የአንድ ሌሊት የጊዜ ገደብ እንኳ አይፈጅም፡፡ጥያቄዎቹ እጅግ ግልፅ፣ ቀላል እና ለዘመን ዘመናት በራሱ አባት ተቋም ልቡ የቆሰለውን ሙስሊም ኅብረተሰብ ቁስሉን በማከም አገራችን የያዘችውን ልማት በተጠናከረ መልኩ ማስቀጠል የሚቻልበትን ጠንካራ ጡንጫ መፍጠር ያስችል ነበር፡፡ ሆኖም የምናየው ነገር የተገላቢጦሽ ሆኖ መንግስት እንደ አባት በመሆን ይህን ሚናውን እንዲጫወት ሲጠበቅበት በተቃራኒው ሕዝብ መንግስትን በልጦ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ልቡ ይበልጡኑ ቆስሏል፡፡ ያቀረበው ሀይማኖታዊ የመብት ጥያቄ ምላሽ መነፈጉ ሳያንሰው መንግስት ራሱ ህጋዊ ሲለው የከረመውን አካሄድ ህገ-ወጥ አድርጎ ሲፈርጀው፣ በህግ አግባብ የሰየማቸውን ወኪሎቹን ህገ ወጥ ከማለቱም ባሻገር ሲያስፈራራ፣ ሲዝት፣ ሲያግት፣ሲያንገላታ እና ሲያስር ማየቱ፣ በህዝብ ግብር የሚተዳደሩ የህዝብ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” አይነት ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ሲያሰራጭ ከዚህ የበለጠ ህዝብን ቅር የሚያሰኝ፣ህዝብን የሚያስኮርፍና የሚያስቆጣ ተግባር የለም፡፡ 
መንግስት በአሁኑ ሰዓት እየተገበረው ያለው ስራ አስነዋሪ ነው፡፡ ሕገ ወጥ ነው፡፡ በእጁ ያለውን የህዝብ አደራ ያለ አግባብ በመጠቀም ላይ ይገኛል፡፡ ይህም የለየለት ሆኗል፡፡ ለዚህ ሁሉ አስነዋሪ እና ህገ ወጥ ተግባሩ የሚገባው የህዝብ ምላሽ ተመጣጣኝ መሆን ይገባው ነበር፡፡ ሆኖም ህዝበ ሙስሊሙ እያሳየ የሚገኘው ንቃትና ጨዋነት የተሞላበት አኩሪ ስነ-ምግባር መንግስትን ከዚህ በላይ እንዳይጓዝ እንቅፋት ሲሆንበት ታይቷል፡፡ ይህም ለመንግስት አካላት የራስ ምታት ሆኖባቸዋል፡፡ ምናልባት ይህ የሐይማኖት ጉዳይ መሆኑን ዘንግተውት ይሆናል፡፡
ከባለፈው ሳምንት ዕሁድ ወዲህ ነገሮች በፍጥነት እና ባልተፈለገ አቅጣጫ እየተሾፈሩ ይገኛሉ፡፡ ህጋዊ ወኪሎቻችን በያሉበት ቦታ ታግተዋል አሊያም ታስረዋል፡፡ “እኛ የህዝብ አደራ የተሸከምን ሰላማዊ ዜጎች ነን፣ ህግ ጥሳችኋል ካላችሁና በህግ ፊት ከፈለጋችሁን ወከባ፣ሽብርና ዛቻ እንዲሁም ማስፈራራት አያስፈልጋችሁም፣ ለዚህ ስትሉ ስራ አትፍቱ የመኪና ነዳጅም አታባክኑ ሙሉ አድራሻዎቻችንን እንካችሁ በደቂቃ ውስጥ እኛው ራሳችን እናንተው ድረስ እንመጣላችኋለን” የሚል ድንቅ ንግግር ከወኪሎቻችን ቢነገራቸውም የደህንነት እና የፀጥታ አካላት እየወሰዱት ያሉት እርምጃ አሳፋሪ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የህዝብን የገነፈለ ቁጣ የሚጋብዝ ቢሆንም ህዝበ ሙስሊሙ ከነቃ ውሎ አድሯልና ነገሮችን በትዕግስት እና በሰከነ ሁኔታ መመልከትን መርጧል፡፡ 
ህዝብ ሙስሊሙ ምንም እንኳን የመንግስትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የሚያስተባብልበት ሁነኛ የመገናኛ መንገድ ባያገኝም ኢቴቪን እንደመልካም አጋጣሚ ይጠቀምበታል፡፡ የሚለፍፈውን በሀሰት መረጃ የታጨቀ ፕሮፓጋንዳ ላለመስማት ቴሌቪዥን ዘግቶ መቀመጥን እንደ ብቸኛ አማራጭ የወሰዱ በርካታ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ ሁሉ ግድ ሆኖባቸው ከጣቢያው ሥርጭት ጋር የተገጣጠሙቱ ደግሞ የሚሰሙትን በተቃራኒው በመረዳት እውነታውን ይደርሱበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዘመን አመጣሹ የኢንተርኔት መረብ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ አሁን አሁን “ፌስ ቡክ ላይ ምን ተባለ?” በማለት የማይጠይቅ ሙስሊም የለም፡፡ ይህንን እውነታ በመረዳት የሚመራው አካል እውነታነታቸው የተረጋገጡትን፣ ፍጹም ከፀብ ጫሪነት፣ ከአመጽ ቀስቃሽነት እና ውለ ቢስ ከመሆን የራቁ መረጃዎችን በትኩሱ ከታማኝ ምንጮች በመውሰድ ለህዝቡ ያደርሳል፡፡
ሆኖም ኢንተርኔት ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊደርስበት የሚችል እንደመሆኑ መጠን ውዥንብር በመፍጠር ህዝቡን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ሊመሩት የሚችሉበት አጋጣሚ እጅግ ሰፊ ነው፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ በዚህ አጋጣሚ እነኚህን አካላት ጠንቅቆ ሊለያቸው ይገባል፡፡ለዚህም ዋነኛ መለያ ሊሆን የሚችለው የሰላማዊ ትግላችን ሂደት ፍፁም ሰላማዊና እና ከአመጽ የፀዳ መሆኑ መለያው ሲሆን ይህንን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የመናድ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች መተላለፍ ሀሰተኛ እና የትግሉ አካል ያልሆኑ መሆናቸውን በቀላሉ መለየት ይቻላል፡፡
ለምሳሌ “ዛሬ ተቃውሟችንን በዝምታ እንግለፅ” ሲባል በተቃራኒው “በተክቢራ ይደምቃል!” ወዘተ የሚሉ እና በሞባይል አጭር መልዕክት አማካይነት “ነገ ሁላችንም የስራ ማቆም አድማ እናድርግ” አይነት መልዕክቶች የሰላማዊ ትግላችን አካል አይደሉም፡፡ በመሆኑም መሰል መልዕክቶችን በጥንቃቄ ልንመለከታቸው ይገባል፡፡
በተጨማሪም ኮሚቴዎቻችን በአሁኑ ሰዓት በእስር ላይ አሊያም በእግት ላይ መሆናቸውን እያወቅን በኢንተርኔት አለም የነሱን አድራሻ በመጠቀም በእነሱ ስም መልዕክት ለማስተላለፍ የሚደረግ ሙከራም አለ፡፡ ምንም እንኳን የሚያስተላልፉት መልዕክት ተቀባይነት እንዲኖረው ወደ እውነት የተጠጋ ቢመስልም አሁንም በጥንቃቄ ልንመለከተው ይገባናል፡፡ በተለይም መልዕክቱ ወደ አመጽ እና ረብሻ እንዲሁም ወደ ጥፋት የሚያዝ ከሆነ አይደለም በእንዲህ ሁኔታ እያሉ ይቅርና የነፃነት አየር በሚተነፍሱበት ሰዓት ከወኪሎቻችን አንደበት የሚፈልቁት ቃላት ሰላማዊ እና ሕጋዊ ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህም ይህ መልዕክት ከጀርባው ሰይጣናዊ አንደምታ ያለውና ከኮሚቴዎቻችን እንዳልሆነ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡
ትግላችን በኮሚቴዎች መታሰር ምክንያት ሊዳፈን አይችልም፣ይቀጥላል፡፡ኢንሻ አላህ! ጉዟችን ተጀመረ እንጂ አልተቋጭም፡፡ ትግላችን መለያ ባህሪው ፍጹም ሰላማዊነቱ እና ቀጣይነቱ ሲሆን ማረፊያው ደግሞ ያነሳናቸው ሶስት መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸው ብቻ ይሆናል፡፡ የህዝቡን የልብ ትርታ የተከተሉ እና ወደ ምንፈልገው ግብ ሊደርሱን የሚችሉ ሰላምንና መረጋጋትን አደጋ ላይ የማይጥሉ እንዲሁም የትግላችንን ቀጣይነትና ውጤታማነት የሚያረጋግጡ ስትራቴጂዎች ይፋ ይሆናሉ፡፡ኢንሻ አላህ፡፡ እነኚህን በመከተል ተሰሚነታችንን እናረጋግጣለን፣ ያለምንም ኪሳራ መብታችንን እንጎናጸፋለን፡፡ ኢንሻ አላህ፡፡
አላህ ይወፍቀን፡፡
Be the first to comment

Latest Articles

Most Popular