be america ye haymanot netsanet derjet yawetawu megelecha mulu tergum

11/8/2012
ከአሜሪካ መንግስት አለም አቀፍ የሃይማኖት ነጻነት ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ

‹‹በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው የሃይማኖት ነጻነት መብት ጥሰት ያሳስበናል››

በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ ከቀን ወደቀን እየጨመረ የመጣው የሃይማኖት ነጻነት መብት ጥሰት ድርጅታችንን (የአሜሪካ መንግስት አለም አቀፍ የሃይማኖት ነጻነት ኮሚሽን) በጣም ከሚያሳስቡት ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ከጁላይ 2011 ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ አስቀድሞ የነበረውን የሃይማኖት አንጃ ለመቀየር የጣረ ሲሆን ሂደቱን የተቃወሙ የሃይማኖት አባቶችን እና ሰባኪዎችንም እየቀጣ ይገኛል፡፡ በሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የተሳተፉ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ሲታሰሩ ቆይተዋል፡፡ በ 29 ኦክቶበር 2012 መንግስት ዘጠኝ ያህል ተቃዋሚዎችን በሽብርተኝነት እና ኢስላማዊ መንግስት ለማቋቋም ሙከራ በማድረግ ወንጀል ከሷቸዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ አንድን የሃይማኖት አንጃ በግድ በመጫን ሃይማኖታዊ አተገባበሮችን ለመቆጣጠር የሚያደርገው ጥረት ያስነሳበትን ተቃውሞ ለማስቆም የኢትዮጵያ መንግስት ካደረጋቸው ሙከራዎች ውስጥ ይህኛው በጣም አሳሳቢው ነው›› ይላሉ የአሜሪካ መንግስት አለም አቀፍ የሃይማኖት ነጻነት ኮሚሽን ኮሚሽነር አዚዛ አል ሂብሪ፡፡ ‹‹የተከሰሱት ግለሰቦች ህገ-መንግስታዊ እና በአለምአቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጣቸውን የሃይማኖት ነጻነት መርሆዎች መጣስ በመቃወም ድምጻቸውን ሲያሰሙ ከነበሩ አስር ሺዎች መካከል አባል የሆኑ ናቸው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት በሙስሊሞች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን አቁሞ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና በአስቸኳይ ያላግባብ የተከሰሱትን ግለሰቦች ሊፈታ ይገባል›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ በአብዛኛው የሱፊ መስመር ተከታይ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ካለፈው ጁላይ 2011 ጀምሮ አል አህባሽ የተባለውን የሃይማኖት አንጃ በግድ ለመጫን ሙከራ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምርጫንም ራሱ በሚፈልገው መልኩ አካሂዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር የዋለ እንደሆነ ተደርጎም ይታሰባል፡፡ በመንግስት እየተፈጸመ ያለው እስራት፣ የሽብርተኝነት ክስ እና የመጅሊስ ምርጫ ቁጥጥር ማስረጃ ሆኖ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ነጻነት አደጋ ውስጥ መግባቱንና መንግስትም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን የመቆጣጠር ፍላጎቱ እያደገ መምጣቱን ነው፡፡
‹‹የአሜሪካ መንግስት ለሃይማኖት ነጻነት ጥበቃ የሚሰጠውን የአገሪቱን ህገ መንግስት እና አለምአቀፍ ድንጋጌዎች ማክበር እንዳለበት ለአዲሱ የኢትዮጵያ አስተዳደር ማስገንዘብ ይኖርበታል፡፡ የአሜሪካ መንግስት አለም አቀፍ የሃይማኖት ነጻነት ኮሚሽን አክራሪነትን በመዋጋት ስም ሃይማኖታዊ ጭቆና ማድረስ የበለጠ ወደአክራሪነት የሚገፋ፣ አለመረጋጋትን የሚፈጥር እና ወደብጥብጥም የሚመራ መሆኑን ይረዳል›› የሚሉት ደግሞ የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ካትሪና ላንቶስ ስዌት ናቸው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ካላት ጂኦ ፖለቲካዊ አስፈላጊነት እና ሙስሊሞችም ከአገሪቱ ጠቅላላ ህዝብ አንድ ሶስተኛ ያህል እንደመሆናቸው መንግስት የሃይማኖት መብት ጥሰቱን አቁሞ ሃይማኖታቸውን በሚፈልጉት መልኩ እንዲተገብሩ ሊፈቅድላቸው ይገባል፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ለአደጋ ተጋላጭ የሆነው ይኸው ክልል ወደበለጠ አለመረጋጋት የሚሸጋገርበት እድል ሰፊ ነው›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የጉዳዩ የኋላ ታሪክ

ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው የሚተገበረው የሱፊ እስልምና መስመር መሆኑ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 27 ደግሞ ለሃይማኖት ነጻነት ጥበቃ የሚሰጥ ሲሆን መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ እንዳይገባ ይደነግጋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ግን አገሪቱ ውስጥ ‹‹ወሀቢዝም›› እየተስፋፋ መጥቷል በሚል እሳቤ ከሊባኖስ የሃይማኖት ምሁራንና ኢማሞችን በማምጣት ለተማሪዎቻችው እና ተከታዮቻቸው ያስተምሩ ዘንድ ለኢትዮጵያውያን ኢማሞች እና መምህራን ስልጠና እንዲሰጡ አድርጓል፡፡ ስልጠናውን ለመውሰድና ለማስተማር ያልፈቀዱ ኢማሞችን ከስራቸው ያባረረ ሲሆን መስጊዶችንና ትምህርት ቤቶችንም ዘግቷል፡፡ ይህንን በመቃወም ነው እንግዲህ በየአርብ ስግደቶቹ ላይ በተለያዩ መስጊዶች ሰላማዊ ተቃውሞ ሲደረግ የቆየው፡፡ ተቃውሞዎቹ በአገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄዱ የቆዩ ቢሆንም ማእከል ያደረጉት ግን የአዲስ አበባውን አወሊያ ትምህርት ቤት እና መስጊድ ነበር፡፡

ተቃውሞዎቹ ሲቀጥሉ ባለፈው ጸደይ ህዝቡ 17 ታዋቂ ግለሰቦችን በአስታራቂነት (በመፍትሄ አፈላላጊነት) በመምረጥ ከመንግስት ጋር ድርድር እንዲያደርጉ ልኳል፡፡ ድርድሩም በሚከተሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ነበር፡- 
1. መንግስት ለሃይማኖት ነጻነት ጥበቃ የሚሰጠውን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ እንዲያከብር
2. መንግስት አል አህባሽ የተባለውን አንጃ በሙስሊሙ ላይ በግድ መጫኑን እንዲያቆምና አህባሽ እንደማንኛውም ሃይማኖት በራሱ ብቻ እንዲንቀሳቀስ
3. የተዘጉ መስጊዶችና ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ዱሮ ለነበሩት ኢማሞችና አመራሮች እንዲመለሱ
4. ለመጅሊስ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድና የሚካሄድበት ቦታም የመራጩን ህዝብ ውሳኔ ለማክበር ሲባል በቀበሌዎች እንዲሆን 

ሆኖም ድርድሩ ሳይሳካ በመቅረቱ ተቃውሞዎቹ በመጠንና በተደጋጋሚነት ጨምረው ነበር፡፡ በምላሹ የኢትዮጵያ መንግስት የታጠቁ ሃይሎችን አሰማርቶ ከበባ በማድረግ እና ቤት ለቤት ፍተሻዎችን በማካሄድ ሰላማዊ ሙስሊሞችን ለማስፈራራት ሲሞክር ቆይቷል፡፡ መንግስት ከጁላይ 13 እስከ 21 የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን እና በትንሹ ሰባ ያህል ተቃዋሚዎችን ማሰሩን የገለጸ ቢሆንም ተቃዋሚዎች ግን የታሰሩት ቁጥር በመቶዎች የሚቆጠር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ተቃዋሚዎች በታሰሩበት ሂደትም ሆነ በእስር ቆይታቸው ወቅት ፖሊስ ትርፍ ሃይል መጠቀሙንም የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ገልጸዋል፡፡ ከታሰሩት ብዙዎቹ በአሁኑ ወቅት ተለቀዋል፡፡ ዘጠኝ የኮሚቴው አባላት ግን አሁንም በእስር ላይ ነው የሚገኙት፡፡ 

በኦክቶበር 29 መንግስት በተቃዋሚዎቹ እና በዘጠኝ የኮሚቴው አባላት ላይ ያቀረበው ክስ የመጀመሪያው ሲሆን ግለሰቦቹ ሲታሰሩ የተወሰዱትም የፖለቲካ እስረኞች ወደሚታሰሩበት እና ተደጋጋሚ ቶርቸር ወደሚፈጸምበት የፌዴራል ፖሊስ ማቆያ ማእከላዊ ነው፡፡ የተከሰሱትም ሽብርተኝነትን ከመከላከል ይልቅ ተቃውሞን ለመደፍጠጥ ጥቅም ላይ ሲውል በቆየው የጸረ ሽብር ህግ ነው፡፡ 

ተቃዋሚዎቹ ቢጫ እና ነጭ ካርዶችን በማሳየት ሰላማዊነታቸውን እንዲሁም እስራትና ክሱን መቃወማቸውን ሲያሳዩ ቆይተዋል፡፡ በጥቅሉ ተቃውሞዎቹ በአብዛኛው ሰላማዊ ነበሩ ሲሆኑ በአንዳንድ ቦታዎች ግን ሰላም አደፍራሽ ክስተቶች ታይተዋል፡፡ በኦክቶበር 21/2011 ተቃዋሚዎችን ከፖሊስ ጣቢያ ለማስፈታት በተደረገ ሙከራ 4 ያህል ሰዎች ሲገደሉ በአፕሪል 2012 ደግሞ ‹‹አህባሽን አላቀነቅንም›› ያለ ኢማም በመባረሩ ምክንያት በተነሳ ተቃውሞ 5 ያህል ሰዎች ተገድለዋል፡፡ 

የድርጅቱን ኮሚሽነር ቃለ መጠይቅ ለማግኘት የሚከተለውን አድራሻ ይጠቀሙ፡- Samantha Schnitzer at sschnitzer@uscirf.gov or (202) 786-0613.
Be the first to comment

Latest Articles

Most Popular