ዶ/ር ሽፈራው AHBASH LE MUSLIMU YETEMERET NEWU BEMALET BEDEFRET TENAGERE BETAM YASAZENAL
መንግሥት ከእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር በመተባበርም ዋህቢያ የሚቃረን የአህባሽ ትምህርት ለአማኙ እንዲሰጥ እየተደረገ ነው
ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ዋህቢያ የሚባለውን አስተምሮ የሚያራምዱ ወገኖች በሕገ መንግሥቱ የሰፈሩ የእምነት ነፃነቶች እየጣሱ ነው፣ እስላማዊ መንግሥት እንዲቋቋም ይፈልጋሉ በሚል በአክራሪነት ፈርጆ ዕርምጃ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
ከእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር በመተባበርም እሱን የሚቃረን የአህባሽ ትምህርት ለአማኙ እንዲሰጥ እየተደረገ ነው፡፡ የዋህቢያ አስተምህሮ መፍለቂያ በሚባለው አወልያ የትምህርት ማዕከልም አንዳንድ ለውጦች እያደረገ መሆኑን ይናገራል፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥት ተቃውሞም እየቀረበበት ነው፡፡ ይህም በእምነቱ ተከታዮች መካከል ውዥንብር እየፈጠረ ሲሆን፣ ጉዳዩን በኃላፊነት ወስዶ እየተንቀሳቀሰ ያለው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሲሆን፣ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያምን በወቅታዊው የእስልምና እምነት ውስጥ በተከሰቱ ውዝግቦችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የማነ ናግሽ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከሚታየው ሁኔታና ከሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አንፃር መንግሥት የያዘውን አቋም ቢያብራሩልኝ?
ዶ/ር ሽፈራው፡- ትልቁና እንደ መንግሥት እየተወያየን ያለነው ጉዳይ አቋማችን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በማክበርና በማስከበር ላይ የተመሠረተ መሆኑን ነው፡፡ በሃይማኖት ተቋም ውስጥ ያሉ የእምነቱ ተከታዮችና ሊቃውንት ከሃይማኖታቸው ተነስተው የሚያብራሯቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ እንደ መንግሥት እኛ የምንገልጻቸው ነገሮች ግን ሙሉ በሙሉ ሕገ መንግሥታችንን በማስከበርና በማክበር ዙሪያ ላይ የሚያጠነጥኑና በዚያው የተወሰኑ ናቸው፡፡ ከዚያ የሚወጡበት አንዳችም መንገድ የለም፤ ሊወጡም የሚችሉ አይደሉም፡፡ በዚህ መሠረት ሦስት የሕገ መንግሥታችን መሠረታዊ የእምነት ድንጋጌዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው በአገራችን የእምነት ነፃነት የተከበረ ነው የሚል ነው፡፡ የዜጎቻችን የእምነት ነፃነት በምንም ዓይነት መገደብ አይቻልም፡፡ ሁለተኛው በአገራችን ያሉ ሃይማኖቶች እኩል ናቸው፡፡ አንደኛው ከሌላኛው አይበልጥም፣ አያንስም የሚለው ነው፡፡ ሦስተኛው መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚል ነው፡፡ መንግሥታዊ ሃይማኖት ወይም ሃይማኖታዊ መንግሥት የሚባል የለም ለማለት ነው፡፡ እነዚህ መርሆዎች አንድ ላይ ተደምረው የዲሞክራሲያዊ ሥርዓታችን መገለጫዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንዱ እንኳን ቢጎድል የተሳካ ሊባል አይችልም፡፡ አንዱ ቢጎድል ዲሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ተጨናግፏል፤ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታችን ተጥሷል ወደሚል ነው የሚወስደን፡፡ እንግዲህ የመንግሥት ኃላፊነት በእነዚህ ሦስት ጉዳዮች ላይ የተቀመጠ ነው፡፡ እነዚህ ሦስቱ መሠረታዊ መርሆዎች እንደተጠበቁ ሆነው ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት፣ ፀረ ዲሞክራሲ የሆነ ድርጊት መፈጸም ክልክል ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱም ይደነግጋል፡፡ ምን ማለት ነው? ለምሳሌ የእምነት ነፃነት የግለሰቦች ነው፣ የዜጎች ነው፣ ማንም አያስገድድም ብለናል፡፡ አንደኛው የሌላኛውን ሃይማኖት ተከታይ የእኔን እምነት ካልተከተልክ ብሎ ማስገደድ ከጀመረ የሰላም መደፍረስ አለ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው የግለሰቡ ዲሞክራሲያዊ መብት ተጥሷል፡፡ ዲሞክራሲያዊ መብት በሚጣስበት ወቅት፣ ሰላም በሚደፈርስበት ጊዜ መንግሥት ቁጭ ብሎ ሊያይ አይችልም፡፡ የመንግሥት አንዱ ተልዕኮ ሁላችንም እንደምናውቀው የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ማስከበር ነው፡፡ ሁለተኛው የሁለት እምነቶችን እኩልነት የሚመለከት ነው፡፡ ሃይማኖቶች እኩል ሆነው ሲያበቁ የእኔ ሃይማኖት ነው የበላይ፣ የአንተ ሃይማኖት ነው የበታች እያሉ ሰዎች ኹከት፣ ብጥብጥና ግርግር ውስጥ የሚገቡ ከሆነ ሁለቱንም ይጥሳል፡፡ ሰላምን ያደፈርሳል፣ ዲሞክራሲን ይንዳል ማለት ነው፡፡ በዚህ ሒደት ልማትም ይስተጓጎላል፡፡ ዜጎች በድህነትና በኋላቀርነት ላይ መዝመታቸው ቀርቶ፣ ብዙኅነታቸው የእምነታቸው ጉዳይና ዋናው ትኩረታቸው ስለሚሆን ይህንን መብታቸውን ለማስከበር መንቀሳቀሳቸው አይቀርም፡፡ በአገራችን ረዥም ትግል የተካሄደው ይህንን ባለመቀበላችን ነው፡፡ ሰላምን፣ ዲሞክራሲንና ልማትን ተቃርኖ የሚቆም ነገር ሲገኝ ዜጎች ለመንግሥት በሰጡት አደራ መሠረት ለመከላከልና ለማስጠበቅ መንቀሳቀሱ ግድ ነው፡፡ ይህንን ባያደርግ ደግሞ የሚያስጠይቀው ነው የሚሆነው፡፡
በአገራችን ያሉት ሃይማኖቶች የቆየ ታሪካቸው ተቻችለው፣ ተባብረውና ተደማምጠው መኖር ነው፡፡ በእስልምናም በክርስትናም ሃይማኖቶች እንደዚህ ነው፡፡ ምናልባትም መንግሥታት ለራሳቸው ግዛትና ንግድ ለማስፋፋት ጭምር ሃይማኖትን እንደ መግቢያ አድርገው ለመውሰድ በሞከሩበት ጊዜ ጭምር አንደኛው ሌላኛውን እየሸፈነ፣ እየተከላከለና አንዱ ሌላውን ሲንከባከብ ለመቆየቱ ታሪክ የነበረን አገርና ሕዝብ ነን፡፡ በዚያ ውስጥ አሉ የሚባሉ ቅሪት አስተሳሰቦችም ጭምር በሒደት እየተስተካከሉ መጥተው በሕገ መንግሥታችን መቋጫ ያገኙበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እንደዚያም ሆኖ በሁሉም ሃይማኖቶች አካባቢ ቀደም ሲል ያነሳናቸውን መርሆዎች የሚፃረር እንቅስቃሴዎች ጠፍተዋል ማለት አይቻልም፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት ከዚህ የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት መርህ አንፃር ዋህቢያ የተባለውን እንቅስቃሴ በአክራሪነት ሲፈርጅ ከምን ትንታኔ በመነሳት ነው?
ዶ/ር ሽፈራው፡- በቅርብ ጊዜያት ፊት ለፊት አፍጥጦ የመጣው በእስልምና ሃይማኖት ሽፋን እየተደረገ ያለው የዋህቢያ እንቅስቃሴ መሠረቱ ረዥምና ሰፊ ነው፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ አካባቢ ገና ከመነሻው መሐመድ ቢን አብዱል አልዋህድ የሚባሉ የሃይማኖቱ የመጀመርያ ፈላስፋ ተብለው የሚጠቀሱ የእምነቱ አባት፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ ከነበረው መንግሥት ጋር ተደራድረው የመሠረቱት ነው፡፡ በሰውዬው ስያሜ ተመሥርተው ዋህቢያ ብለው ሲያስፋፉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በመንግሥት ክንፍ መንግሥታዊ ሃይማኖትን በንጉሣዊ ቤተሰብ ሥልጣን ይዘው ቆይተዋል፡፡ ስለዚህ ሲወርድ ሲዋረድ የጋራ መግባቢያ ሰነድ እየተፈራረሙ በአንድ በኩል መንግሥት ዋህቢያን እንዳይነካ፣ በሌላ በኩል ዋህቢያ መንግሥትን እንዳይነካ በጋራ የሚኖሩበት ሁኔታ ነበር፡፡ ስለዚህ ዋህቢያና የአብዱል አልዋህድ ልጅ፣ የንጉሣዊያን ቤተሰቦች የልጅ ልጆች አንደኛው አንደኛውን ጠብቆ በመኖር የጋራ መግባባት ፈጥረው የሄዱበት ነው፡፡ ይኼ እምነት በሳዑዲና በሌላ ቦታ ባለው ሲወሰድ አንዱና የመጀመርያው መንግሥታዊ ሃይማኖት መሆን ነው፡፡ ስለዚህ የዋህቢያ ዋና መነሻውና መደምደሚያው “መንግሥታዊ ሃይማኖት ካልሆንን በስተቀር በአንድ አገር ውስጥ ሃይማኖት አለን ማለት አንችልም፡፡ እኛ የምናምነውን የማይከተል በሙሉ ሙስሊም አይደለም፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው በሙሉ እንደሰው ሊቆጠር የማይችል ከሃዲ ነው፡፡ ስለዚህ መጥፋት አለበት፤” ብሎ የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ዋህቢያ የእምነት ነፃነትን አያስተናግድም፤ በራሱ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ሌሎች የትኛውም ዓይነት የእስልምና “ሴክቶች” መኖር የለባቸውም የሚል ነው፡፡ መጥፋት አለባቸው ብሎ ነው የሚሄደው፡፡ ይኼ የእምነት ነፃነትን የሚጋፋ ነው፡፡ ሌሎች ውስጥ ያሉ አማኞች ሰላም ሲሏቸው እንኳን “ሂዱ መጀመርያ ሰልማችሁ ኑ” በሚል የሚፈርጁና ከመንግሥት ጋር ባለው ማንኛውም ግንኙነት ደግሞ እስላማዊ ካልሆነ መንግሥት ጋር ትብብር ፈጥራችኋል ስለዚህ ከሃዲ ናችሁ በማለት በማስገደድ ጭምር ሌሎች ሴክቶችን መጀመርያ በማባበል፣ ከዚያ በማስፈራራት፣ ካልሆነ እስከ መግደል ድረስም ጭምር በመሄድ ወደ ራሱ ሴክት ለመቀየር የሚረባረቡ ኃይሎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሦስቱን ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎች የሚቃረን አስተሳሰብ ነው፡፡ እኛ እንደሱ ያለ ፍልስፍና አይደለም እያራመድን ያለነው፡፡ እኛ የምናራምደው ፍልስፍና ሕገ መንግሥታችን ነው፡፡ ከዚህ ተነስተን ነው ዋህቢያ ማለት አክራሪ ተቋም ነው፡፡ ይህንን አክራሪነትን በመተው በይፋ ሕገ መንግሥታችንን እንቀበላለን ብሎ አውጆ ከገባ እኛ ከዋህቢያ ጋር ነገር የለንም፡፡ መንግሥትም ሙስሊሙን ሕዝብ እየጠየቀ ያለው እነዚህ መርሆችን አክብሮ፣ የየትኛውንም ሃይማኖት መኖርን ለሕዝቡ ግልጽ አድርጎ ራሱን በዚያ መርህ መርቶ መሄድን ነው፡፡ “የእኛ እስልምና የመንግሥት ሃይማኖት ካልሆነ በስተቀር እዚች አገር ውስጥ ካለ አክራሪ (ከሃዲ) መንግሥት ጋር ተባብረን መኖር አንችልም፡፡ ስለዚህም ዋናው መፍትሔ መታገል መታገል ነው፤” የሚለው፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት የአህባሽ ትምህርት (ሥልጠና) በሊባኖስ ኡላማዎች እንዲሰጥ እያመቻቸ ነው፡፡ የመንግሥትን ዕርምጃ የሚቃወሙ የእምነቱ ተከታዮች በበኩላቸው፣ ሁለቱም አስተሳሰቦች እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የኖሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ መንግሥት አንዱን ጎራ ለይቶ ሌላውን ለማዳከም እየሠራ ነው፤ በሃይማኖታችን ጣልቃ በመግባትም ሕገ መንግሥታዊ መርሁን ጥሷል ይላሉ፡፡
ዶ/ር ሽፈራው፡- ለያይተን ብናያቸው ጥሩ ነው፡፡ አህባሽን በሚመለከት አህባሽ የሚባል ሃይማኖትም ሴክተርም የለም፡፡ ይኼኛው ዋህቢዮችና የዋህቢያ ድምፅ የሚያስተጋቡት፣ አንዳንድ የግል ጋዜጦች ለማደናገር ይጠቅማል በሚል በስፋት ያሰመሩበትና ሕዝበ ሙስሊሙን እስከማደናገር ድረስ የሄዱበት ጉዳይ ነው፡፡ አህባሽ የሚባለው የዓረቦቹ አገላለጽ በንጉሡ ዘመን (እንደሚታወቀው ሃይማኖቶች በእኩል የማስተናገድ ችግር ስለነበር) ሃይማኖታቸውን ሊያስፋፉ የሚችሉበት ዕድል ስላልነበር፣ በሞከሩበት ወቅትም በእስር እንዲቆዩና የቁም እስረኛ ተደርገው፣ በኋላ በስደት ለቀው የሄዱ ሼክ አብዱላሂ የሚባሉ የሐረሪ ተወላጅ ማለት ነው፡፡ ሼክ አብዱላሂ ኢትዮጵያዊ እንደመሆናቸው (ዓረቦቹ ከኢትዮጵያ የሄደውን ሰው በሙሉ አህበሽ ነው የሚሉት) ከእሳቸውም ጋር በተያያዘ የሚሰጡት ትምህርት የአክራሪነት አስተሳሰብን በቅዱስ ቁርዓንና ሐዲስ አስተሳሰብ ቀይረው ማስተማር በመቻላቸው ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝተው፣ ትምህርቱንም አስፋፍተው በዓለም ደረጃ ወደ 54 አገሮች አካባቢም ጭምር የሚያስተምሩት ነው፡፡ ትምህርቱም ነባር የእስልምና እምነት የሚከተላቸው አስተምህሮዎችን ነው፡፡
ተለየ ተብሎ የሚቀርብ ነገር የለም፡፡ ተለየ ተብሎ የሚገለጸው አህባሽ የሚባለው አገላለጽ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ምሁር ከወሰዱት በኋላ ሊቃውንት ለአገራችን መልሰው አምጥተው ያስተማሩት ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ የአቀራረብ ጉዳይ ካልሆነ መሠረታዊ የእስልምና ሃይማኖት አባቶችና ምሁራን እንደሚናገሩት ከእምነት የወጣ ነገር አይደለም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሃይማኖቶች የተለያዩ ምሁራንን እያስመጡ ያስተምራሉ፡፡ ለምሳሌ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ብንወስድ ከህንድ፣ ከግብፅ፣ ከሶሪያና ከተለያዩ መሠረታዊ የእምነቱ እውቀት አለ ብለው ከሚያስቡዋቸው አገሮች መምህራንን እያመጡ የሚያስተምሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ዋህቢያም ምንም ማቆሚያ ሳይኖረው ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከፓኪስታን፣ ከአፍጋኒስታንና ከተለያዩ የአክራሪነት አስተሳሰብ ያለባቸው (ከሱዳንም ጭምር) ሰዎች እያመጣ ሕዝበ ሙስሊሙን በማደናገር ሲያስተምር ነው የቆየው፡፡ ስለዚህ እነዚህ በዚህ ዓይነት መንገድ ሲመጡ (ለምሳሌ ከህንድ የመጣ አስተማሪ ሂንዱዝም አምጥተሃል አልተባለም) የተለያየ አገር ዜግነት ይዘው መጥተዋል ያለ ሰው የለም፡፡ ዋናው ሰዎችን ያስተማሩት ትምህርት በእምነት ተከታዮች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶና የሃይማኖት ዕውቀት ይጨምራል በሚል የተወሰደ ነው፡፡ ስለዚህ አዲስ ነገር አይደለም ለማለት ነው፡፡
እዚህ ላይ የተሰጡት ትምህርቶች በምንም ዓይነት መንገድ እንደ ትምህርት ይሰጣሉ እንጂ፣ የግድ ተግተህ ወስደህ በዚህ ላይ ማመን አለብህ ብሎ የሚያስገድድ ሰው የለም፡፡ ይህንን ማድረግ ከሕገ መንግሥታችን ጋር የሚጋጭ ነው የሚሆነው፡፡ አሁን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ያመጣቸው መምህራንም ቢሆኑ በራሳቸው ጊዜ የመጡና ትምህርቱን ያስተማሩ እንጂ፣ ይህንን ትምህርት ካልተቀበልክ በስተቀር የሚሉበት መንገድ የለም፡፡ ኅብረተሰቡ ትምህሩን ይወስዳል፣ መቀበልና አለመቀበል የራሱ መብት ነው፡፡ ስለዚህ በአህባሽ ዙርያ የሚነዙት መደናገሮች የዋህቢያው ቡድን ናቸው፡፡ ይህንን የሚያራምደው አካል ሕዝባችንን በቀላሉ ለማደናገር ያመቸናል ያለው መጤ ሃይማኖት መጅሊሱ አምጥቶ ጭኖብሃል ነው፡፡ ይህ አመለካከት በቀላሉ ሕዝቡ ውስጥ ገብቶ ሊያንቀሳቀስ የሚችል ነው ብለው ያመጡት ጉዳይ ነው፤ ግን ውሸት ነው፡፡ ስለዚህ አህባሽ የሚባል ሃይማኖት የለም፡፡ የእስልምና ጉዳዮች ሲያስተምር የነበረው የነባሩን እምነት ተከታዮች ዕውቀት ለማሳደግ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ አልቀበልም፣ ይህንን ትምህርት አልወስድም የሚል አለመሳተፍ ይችላል፡፡ ትምህርቱንም ወስዶ አይጠቅመኝም ማለት የራሱ ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ዋህቢያ እንደ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ወይ? ከአልቃይዳና ከሌሎች የታጠቁ አሸባሪ ድርጅቶች ጋር ዋህቢያ የሚለይ መሆኑን ወይም አንድነት እንዳለው መንግሥት ምን ያህል አጥንቶዋል? ዋህቢያ አክራሪ ነው ለሚለው ፍረጃስ ተጨባጭ ማስረጃዎቹ ምንድን ናቸው?
ዶ/ር ሽፈራው፡- እስልምና ወደ አገራችን ከገባ ወደ አንድ ሺሕ አራት መቶ ዓመታት ሲያስቆጥር የሚታወቀው በሱፊ-ሱኒ እምነት ነው፡፡ የአገራችን የእስልምና እምነት ተከታይ የሚከተለውም ይኼንን ነው፡፡ በሒደት ግን በተለያዩ ሰዎች አማካይነት የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው አካላት በተለያዩ ሽፋኖች በትምህርትና በማሠልጠን ሽፋን ወደ አገራችን የመጡበት ሁኔታ አለ፡፡ ምናልባትም የዛሬ 25 ወይም 30 ዓመት ይሆናል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ዋናው መተከያው የነበረው (የተለያዩ ቦታዎች እንዳሉ ሆነው) አወልያ የትምህርት ኮሌጅ የሚባለው ነው፡፡ አወልያ ሥራውን ሲጀምር ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለልጆቻችን ይጠቅማል ብለው ያደራጁት ተቋም ነው፡፡ ይህ ተቋም እየሰፋ ሲሄድ፣ በተለይም አንዳንድ የውጭ አገር መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በእገዛና በድጋፍ ስም ተቋሙን እየተቆጣጠሩት ሄደዋል፡፡ በተለይም ዓረብኛ ቋንቋ እናስተምራለን በሚለው የትምህርት ክፍል ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች አባትና እናት የሌላቸውን ወጣቶች በማሰባሰብና በመመልመል፣ የዋህቢያን ትምህርት በቀጥታ ከሙሐመድ ቢን አብደል ውሃብ የተጻፉትን መጻሕፍት በመጠቀም ዝግ በሆነ ሁኔታ በምንም ዓይነት መንገድ ከውጭ እንዳይገናኙ ከውስጥ ብቻ ቆልፈው፣ ወደ ውጭ በሚወጡበት ጊዜ ተናዳፊ እንዲሆኑ አሠልጥነዋል፡፡ እስከዛሬ ከ200 እስከ 300 የሚሆኑ ተማሪዎችን በዚህ ዓይነት መንገድ እስከ አራት ዓመት ድረስ አስተምረው እየተመረቁ እንዲሰማሩ አድርጓቸዋል፡፡ ስለዚህ የሚሰማሩ ተማሪዎች የእስልምና ትምህርት በሚሰጥባቸው የትምህርት ተቋማት መድረሻዎች ላይ ይሰማራሉ፡፡ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ በማስገባት የዋህቢያ አስተሳሰብን በመዝራት ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ እንዲሄድ ያደረጉበት ሁኔታ አለ፡፡ ለዋህቢያ አስተሳሰብ ምንጮች ናቸው ከሚባሉ ውጭ አገር ካሉ ከተለያዩ ተቋማትም ጋር ግንኙነት እየፈጠሩ፣ ለዚህ የሚሆን ሀብት እያመጡ፣ ከሀብቱም ትልቁን ድርሻ ለራሳቸው እያዋሉ፣ ሌላውን ደግሞ የዋህቢያን አስተሳሰብ መግዣ እያደረጉ የተንቀሳቀሱበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ በገንዘብ ነው የሚገዙትና የሚያንቀሳቅሱት የሚለውን ለማስቀመጥ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት በአወልያ የትምህርት ተቋም አንዳንድ ለውጦች ለማድረግ ሲንቀሳቀስ ግን ከፍተኛ ተቃውሞ እየቀረበበት ነው ያለው፡፡
ዶ/ር ሽፈራው፡- በዓረብኛ ትምህርት ሽፋን የሚሰጠውን የአክራሪነት ትምህርት ማቆም አለበት ብሎ መጅሊሱ ሲንቀሳቀስ “አሁን ለመጨረሻ ጊዜ ምሽጋችን ተመታ ማለት ነው፡፡ ይኼ ተመታ ማለት የአይዲዮሎጂው መፍለቂያና ማስተማሪያ ማዕከልና የእኛ ህልውና አበቃ ማለት ነው” በሚል ነው የመጨረሻ የሞት ሽረት አድርጎ የመንቀሳቀስ ሥራ ውስጥ እየተገባ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ በአገራችን ቁጥሩ በጣም ትንሽ የሆነ ነገር ግን በሰፊው ከውጭ በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ አንዳንድ ባለሀብቶችም (ጥቂት ኢትዮጵያውያንም) ባሉበት ነው እየሠራ ያለው፡፡ በተለይም አዲስ አበባ ውስጥ በሚታወቁ ቦታዎች ላይ ዋና ማዘዣ ጣቢያ ሆነው የሚሠሩበት፣ በኦሮሚያም ወደ ስምንት ዞኖች አካባቢ ሰፍረው የሚገኙበት፣ በደቡብ ክልልም አንድ ሦስት አካባቢዎች ላይ በተመሳሳይ ያሉበት፣ በአማራ ክልልም አንድ ሦስት ዞኖች አካባቢ ላይ በስፋት የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ፈጥረው ነው እየሄዱ ያሉት፡፡ ስለዚህ በአገራችን ውስጥ የእምነት ነፃነትን የሚጋፋው የዋህቢያ አመለካከት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴውም አለ፡፡ ምን እየሠሩ ነው ያሉት? ከራሳቸው አመለካከት ተነስተው እነሱን የማይከተለውን በአደባባይ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ለሕልፈተ ሕይወት የሚዳርጉበት ሁኔታ አለ፡፡ የእኔን ሴክት ካልተከተልክ ብለው የሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት በተገቢው የፀሎት በሥርዓት እንዳይፈጸም የሚከለክሉበት ሁኔታም አለ፡፡ የእነሱን ሴክት ያልተከተሉ ሰዎችም ማኅበራዊ መገለል እንዲደርስባቸው የሚደረግበት ሁኔታም አለ፡፡ ብዙ መገለጫዎች አሉት፡፡
በሌላ በኩል የእኔን ሴክት የማይከተል በሙሉ የከፈረ ነው (ከሃዲ ነው)፣ መንግሥትም ጭምር እስላማዊ አይደለም በሚል በትምህርት፣ በጤናና በግብር ከመንግሥት ጋር አንተባበርም፡፡ ወደ ትምህርት ተቋማትም እንዳትሄዱ፣ ከመንግሥትም ጋር እንዳትተባበሩ፣ ግብርም እንዳትከፍሉ በሚል ፀረ ልማት አካሄድም ጭምር የሚፈጽሙበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ “እስላማዊ መንግሥት ነው የምንፈልገው፣ ሃይማኖታችን ነው የሚያዘው” በሚል በአደባባይ የሚሄዱበት፣ በጋዜጦችም ጭምር በይፋ የሚገልጹበት ሁኔታ ጭምር ነው ያለው፡፡ በአንድ ጋዜጣ “ቅዱስ ቁርዓንን ሐዲሳችን ሕገ መንግሥታችን ነው፡፡ ስለዚህ እስላማዊ ያልሆነ ሕገ መንግሥት እኛን አይወክልም፤ እኛ አንገዛበትም፤” በይፋ ያሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ሌሎችም በውይይት መድረኮች በግልጽ የሚናገሩት አሉ፡፡ የመቃብር ቦታዎችን፣ ቤተክርስቲያንና መስጊዶችን በስፋት የማቃጠል ተግባር ይፈጽማሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ሦስት ሳምንታት ደግሞ አወልያን ማዕከል አድርገው የግብፁ “ታህሪር ስኩዌር” እናደርጋለን በሚል ራሳቸውን እያደራጁ፣ በአዲስ አበባም በሌሎች አካባቢዎችም የሚያደራጁበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ይህንን አስተሳሰብ ይዘው መቀጠላቸው ከሕገ መንግሥታችን ውጪ ስለሆነ ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው፡፡ በእርግጥም በተጨባጭ የአገርና የሕዝብ ስጋት ሆኖ ያለ አካሄድ ነው፡፡ “ካርጅያ” የፖለቲካ (አይዲዮሎጂ) ክንፍ ሆኖ የሚሠራ ድርጅት ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የራሱ ተቀጥላ ሆኖ የሚሠራ “ከዋርጅያ” በሚባለው ደግሞ፣ ከሌሎች እየተናበቡ ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር እያበሩ፣ ሰዎች በጣም አሰቃቂ በሆነ መንገድ እየገደሉና እያተራመሱ የሚሄዱበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ለምሳሌ ኦነግ እንደ ኦነግ ሆኖ በመንቀሳቀሱ ሕዝቡ አልቀበል ሲለው፣ በሃይማኖት ሽፋን ከዋርጅያ ሆኖ የኦነግ አስተሳሰብን ለማራመድ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ነበር፡፡ ይኼ በተጨባጭ ሰዎች ራሳቸው ተይዘው በዚያ ውስጥ የተገኙበትና የተፈረደባቸው ሁኔታ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ያም ሆኖ መንግሥት በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ገብቶ እየተጫወተው ባለው ሚና፣ የችግሩን አቅጣጫ ለመቀልበስ እየተከተለው ያለው አካሄድ ትክክል ነው ይላሉ?
ዶ/ር ሽፈራው፡- ዋናው የአክራሪነት ችግር በአገራችን ያለው ድህነትና ኋላቀርነት የሚወልደው ነው፡፡ በሰዎች ድህነት ላይ ዋሃቢዝምን ለማስፈን እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ያለው፡፡ ሁለተኛው የዕውቀት ችግር ነው፡፡ ይኼ በሁለት መንገድ ይታያል፡፡ አንደኛው ሕገ መንግሥታዊ ዕውቀት ነው፡፡ ሁለተኛው ራሱ የዲን (ሃይማኖት) ዕውቀት ነው፡፡ ስለዚህ የዚህ የዋህቢያ እንቅስቃሴ ምን እንደሆነ ሳይገነዘቡ በመደናገር የተቀላቀሉ ዜጎች አሉ፡፡ በአንድ በኩል ሕገ መንግሥታችን ምን እንደሚል ማስጨበጭ፣ በሌላ በኩል የዲኑ ዕውቀት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የተሠራው ሥራም ቢሆን መንግሥት እዚህ ውስጥ ያሉትን ለመፋረድ በሕግና በሥርዓት ከመሄዱ በፊት፣ መጀመርያ በውስጡ የተቀላቀሉትን ንፁኃን ዜጎችን፣ ሆን ብለው ይህንን ሥራችን ብለው ከገቡት የመለየት ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ምን ይላል ብሎ ለዜጎች ማስተማር የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ መንግሥት በተለያዩ ደረጃዎች ሲያደርግ የነበረው እያደረገም ያለው ይህንን ነው፡፡ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁ የገቡ ዜጎች ግን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎቹን ማሳወቅ የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ ቢሆንም፣ ሕዝባችን ያለውን ንቃተ ህሊናና ሌሎች ነገሮችን ታሳቢ በማድረግ መንግሥት ሕገ መንግሥትን ለማስተማር ተንቀሳቅሷል፡፡ ሕገ መንግሥትን ለማስተማር በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ሕገ መንግሥትን በመቃረን መቆም ማለት ምን ማለት እንደሆነና ቆመውስ የተገኙ እነማን መሆናቸውን መናገር ማለት በዚያ ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባት ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ያደረገው ነገር ቢኖር ሕዝባችን ሕገ መንግሥቱን አውቆ ራሱ ዘብ እንዲቆም ለማስቻል፣ በዚህ ዙሪያም ብዥታዎች ካሉም ጠርቶ እንዲወጣ ነው፡፡ ዋህቢያ ራሱ ተለይቶ እንደወጣ ራሱ ገልጿል፡፡ እነማን እንደሆኑ ተለይቶ የታወቀበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ሳዑዲ ዓረቢያ ካለው ዋህቢያ እኛ እንለያለን ብለው ሐሳባቸውን ቀይረው ከመጡ እኛ ጠብ የለንም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዋህቢያ የእምነት ነፃነትን፣ መንግሥትና ሃይማኖት የተለዩ ናቸው የሚለውን መርህ አክብሮ በዚህ መርህ በአመለካከትም በተግባርም ከቀረበ ዛሬውኑ የቤት ሥራችን ተጠናቋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም የመንግሥት ሚና በዋናነት ሕገ መንግሥቱን ማስተማር፣ የዲን ዕውቀቱን በሚማሩበት ወቅት የሰላም፣ የፀጥታና የደኅንነት ጥበቃ ተደርጎ ሊሆን ይችላል፤ ይህም ሕገ መንግሥታዊ መብት የማስጠበቅ ግዴታ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ይኼንን የመንግሥት እንቅስቃሴ የሚቃወሙ መጅሊሱን በአግባቡ ያልተመረጠ ነው አይወክለንም፤ ተቋሙም ሕዝበ ሙስሊምን ለማገልገል አቅም የለውም የሚሉ ቅሬታዎች ያቀርባሉ፡፡ መንግሥት ደግሞ አክራሪ ያለውን ቡድን ለመነጠል ከአንደኛው ወገን ጋር ነው እየሠራ ነው ይባላል፡፡ የመንግሥት የወቅቱ ሚናና ፍረጃ ከዚህ ጋር ተጣምሮ የችግሩን አቅጣጫ አያባብሰውም ወይ?
ዶ/ር ሽፈራው፡- መጅሊሱን አልተመረጠም በሚለው አቀራረብ የምርጫው ጊዜ እንዳለፈበት እኛም እናውቃለን፡፡ የምርጫው ጊዜ ያለፈበት መጅሊስ ቢሆንም፣ በመጅሊሱ ውስጥ ያሉ ሰዎች ግን በምርጫ የመጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም በእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የመጅሊሱ ኃላፊነት ከመስጊድ ጀምሮ ነው የሚመጣው፡፡ አንድ ሰው ሲጎድልም በዚያው ነው የሚተካው፡፡ ስለዚህ አዲስ ሰው (ያለ ምርጫ) ወደ መጅሊሱ የሚመጣበት ዕድል የለም ማለት ነው፡፡ አሁን ያሉት ሰዎች መንግሥት ያመጣቸው ናቸው የሚል ፍረጃ አለ፤ የተሳሳተ ነው፡፡ በየክልሉ ከተመረጡ መጅሊሶች ውስጥ ነው የፌዴራል መጅሊስ የሚመጣው፡፡ ስለዚህ ፌዴራል ላይ እገሌ እገሌ ሁን ተብሎ የሚሠራ ነገር የለም፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን የዋህቢያ አካል መጅሊስን አናውቀውም፣ ስለዚህም በባላደራ ቦርድ ማደራጀት አለብን፣ የመጅሊስ መዋቅርም በምርጫ ሳይሆን በሹመት ነው መቀመጥ ያለበት እስከሚል ድረስ ነው የሚሄደው፡፡
መጅሊሱ ግን ሥርዓት ባለውና ሕዝበ ሙስሊሙን በሰፊው ባሳተፈ መንገድና ከመስጊድ ጀምሮ በሚመጣበት ሁኔታ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን የሚያከብሩ ሰዎች በሚሳተፉበት አኳኋን መምጣት አለበት ብለን ነው የምናስበው፡፡ መጅሊሱንም በተለያዩ ጊዜያቶች ይህንን አቋም ያመላከተበት ጊዜ አለ፡፡
ሌላው መንግሥት ከመጅሊስ ጋር ለምን አብሮ ይሠራል? የሚል ነው፡፡ መንግሥት ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ጋር አብሮ ይሠራል፡፡ አብሮ የሚሠራው ለምንድን ነው የሚለው ነው የሚለየው፡፡ መንግሥት አብሮ የሚሠራው በሚያገባው የሰላም፣ የልማትና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ያሉት ዜጎቻችን ናቸው ሌላ አይደሉም፡፡ እነዚህ ዜጎች (እምነቱ ውስጥ እንዳለው ሌላ ዜጋ) እምነታቸውና ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ይፈልጋሉ፤ ከድህነትና ከኋላቀርነት እንዲላቀቁ ይፈልጋሉ፡፡ መንግሥት የሰላም ፍላጎት አለው፡፡ ሃይማኖቶችም የሰላም ፍላጎት አላቸው፡፡ ልማትም እንደዚሁ፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በሚያገባው ይሠራል፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም ሲባል እያስቀመጥን ያለነው፣ ‘ይህንን ሃይማኖት ነው የምትከተለው፣ ይህንን መጽሐፍ ነው የምትሰብከው’ በሚል ውስጥ ገብቶ ሃይማኖታዊና እምነት ነክ መንፈሳዊ ግንኙነት ላይ ገብቶ አይሠራም እንጂ፣ ከሃይማኖትና ከእምነት ተቋማት ጋር አብረን የምንሠራባቸው አጀንዳዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ከእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም ጋር የሠራነው ሰላምና ልማትን በሚመለከት ነው፡፡ ይህንን በሚመለከት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና ከሌሎችም ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ሁላችንም የሚያገባን የአገር ጉዳይና የሃይማኖት ጉዳይ ስለሆነ አይደለም፡፡ ወደፊትም ከእነዚህ የሃይማኖት ተቋማት ጋር በሚያገባንና በሚያግባባን ጉዳይ ላይ የየራሳቸውን ድንበር ጠብቀን አብረን መሥራታችን አይቀርም፡፡ ምክር ቤቱ አቅም የለውም ለሚባለው የአቅም ችግር የዚሁ ምክር ቤት ብቻ አይደለም፡፡ እኛም እንደ መንግሥት አገራዊ ችግር ነው የምንለው፡፡ አለ የሚባለውን የአቅም ችግር ሕዝበ ሙስሊሙ ነው መጠገንና ማስተካከል ያለበት፡፡ ይኼ የሚጠገነው ደግሞ በምርጫ ወቅት ነው፡፡ ፊት ለፊታችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርጫ ይከናወናል፡፡ በዚያ መሠረት ሕዝበ ሙስሊሙ በአንድ በኩል አቅምንና ብቃት ያላቸውን፣ በሌላ በኩል ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌን የሚያከብሩና የሚያስከብሩ መሆናቸው የተረጋገጠላቸውን የሃይማኖት መሪዎች ወደ ምርጫው እንዲገቡና እንዲመረጡ በማድረግ የሚንቀሳቀስ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እየተሰጡ ያሉት ሥልጠናዎችም ተቋሙ አቅም ኖሮት የሕዝበ ሙስሊሙን ጥያቄ ሊፈታ በሚችልበት ደረጃ ላይ ለማምጣት እንዲያስችሉ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ዋህቢያና ሌሎች መንግሥት በአክራሪነት የፈረጃቸው ድርጅቶች ድጋፍ በብዛት የሚያገኙት ከሳዑዲ ዓረቢያና መሰል ዓረብ አገሮች ነው ብለውኛል፡፡ የአሁኑ ሁኔታና የመንግሥት ሚና ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገሮች ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ አይፈጥርም? ኢንቨስትመንት በመሳብ ደረጃም. . . .?
ዶ/ር ሽፈራው፡- በሳዑዲም ይሁን በሌሎች የመንግሥት አካላት ላይ ይህ የመንግሥት አቋም ነው ብለን አንወስድም፡፡ አስተሳሰቡን በገንዘብ የሚደግፉ አካላት ሊኖሩ ይችላሉ ብለን እናስባለን፡፡ በአንዳንድ ኤምባሲዎችም ውስጥ አንዳንድ ግለሰቦች ይህንን ጉዳይ ከራሳቸው ጥቅም ተነስተው ሊደግፉና ሊያንቀሳቅሱ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡
ስለዚህ ከዋህቢያ ጋር የምናደርገው የፀረ አክራሪነት ትግል ከአገሮች ጥቅም ጋር የሚጋጭ ነገር የለውም፡፡ የራሳችንን ውስጣዊ ሰላማችን፣ የራሳችንን ሕገ መንግሥት ከማስጠበቅ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ወደየትኛውም አገርና የመንግሥት ሥርዓት ሄደን የቀሰርነው ጣት የለም፡፡ ስለዚህ የትኛውንም አገር የሚያስቆጣ ተግባር ነው ብለን አናምንም፡፡ እነዚህ ድጋፍ ያደርጋሉ ተብለው የሚገመቱ ሰዎች ደግሞ በአገር ለአገር ግንኙነት ላይ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ይኖራል የሚል እምነት የለንም፡፡ በኢንቨስትመንትም ላይ ችግር የሚፈጠረው ሰላም በሌለበት አገር ነው፡፡ ትግላችን ሰላማዊ የሆነ አገር ለመገንባት ነው፡፡ አንድ ኢንቨስተር የሚሄደው ሠርቶ አተርፋለሁ በሚለው አገር ላይ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ አገር ከማንም በላይ ሰላም ስትሆን ነው፡፡ ስለዚህ ከዋህቢያ ጋር እያደረግን ያለነው ትግል በዋነኛነት ሰላም እንዳይደፈርስ፣ ልማት እንዲበለጽግና ኋላቀርነት እንዲጠፋ ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ለኢንቨስትመንትም ምቹ ሁኔታ መፍጠርና በሃይማኖት ሽፋን የሚመጡ አክራሪነትን፣ የፖለቲካ ተልዕኮን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ነው እየተሠራ ያለው፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙን የማደናበር ሥራ እየሠሩ ያሉት አክራሪዎች ከጀርባቸው ሌሎችም ኃይሎች እንዳሉዋቸው አውቆ፣ ለሰላሙና ለደኅንነቱ ዘብ ሆኖ እንዲቆም፣ ችግሮች ሲኖሩም እየተመካከርን እንድንፈታ ነው መንግሥት የሚፈልገው፡፡
mengistachin minew endih torinet amarew be giltsi ambageneninetun eyaweje new
allah mewurejawun yafatinew