ከኮሚቴ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ
ግንቦት 2፣ 2004
ለሕዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መፍትሄ ለማፈላለግ ከተቋቋመው ኮሚቴ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ
በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ላለፉት አራት ወራት እጅግ ሰላማዊና ህገ መንግስታዊ በሆነ አግባብ አቤቱታችንን ለመንግስት ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ ጥያቄዎቻችን የሃይማኖት፣ የግለሰብና የማህበረሰብ ነጻነቶችን በተመለከተ በሕገ መንግስታችን የተቀመጡትን አቢይ መነሻዎች፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሁም መብቶችና ነጻነቶችን መሰረት ያደረጉ ህጋዊ የህዝበ ሙስሊሙ ብሶቶች ናቸው፡፡ ጥያቄያችንን ያቀረብነው በህገ መንግስቱ መግቢያ ላይ እንደሰፈረው “ባህሎችና ሃይማኖቶች ካለ አንዳች ልዩነት እንዲራመዱ የማድረ...ጉ አስፈላጊነት ጽኑ እምነታችን” በመሆኑ ነው፡፡ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. መንግስትም ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት የማረም ህገ መንግስታዊ ሀላፊነት እንዳለበት ተስፋ በማድረጋችን ነው፡፡
ጥያቄያችን ሕገ መንግስቱ ይከበር፣ ሃይማኖት በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱሕገ ወጥ እንደመሆኑ ሁሉ መንግስትም በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ስልጣንስሌለለው በዚህ ረገድ ባለስልጣናቱንና መዋቅሩን ይቆጣጠር የሚል መንፈስ ያስተጋቡ ሰላማዊ የመብት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ሕገ-መንግስቱን የሚያከብርና የሚያስከብር የራሱንም መተዳደሪያ ደንብ የሚያከብር የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትቢዋቀር ኖሮ እኛም ህዝባዊ ጥያቄ በመያዝ የመንግስት ቢሮዎችን ማንኳኳት ባላስፈለገን ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እነዳለ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የህዝባዊ ንቅናቄውን ቀና መነሻና ጥያቄ ለሀገርም ለህዝብም በማይፈይድ መንፈስና ገለጻ ማቅረቡ አሳዝኖናል፡፡
እንደሚታወቀው የካቲት 26፣ 2004 የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሰጠው ምላሽ ውስን የመርህም ሆነ የአፈጻጸም ግልጽነት ያልተስተዋለበት ከመሆኑ ባሻገር መጅሊሱ ሆን ብሎ ሲሰጣቸው የነበሩ መግለጫዎች ህዝባዊ ቁጣበማስከተላቸው የጥያቄያችን ይሰማ ትግላችንን ለመቀጠል መገደዳችን ይታወሳል፡፡
ይሁንና በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር ምንም እንኳ ጥያቄአችንን በቀጥታ መልሰውልናል የሚል እምነት ባይኖረንም መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ እንደማይገባ ዳግም አረጋግጠውልናል፡፡ ተግባራዊነቱን በሂደት የምንታዘበው ጉዳይ ነው፡፡ ወትሮውንም የአፈጻጸም ስህተት እንጂ የመርህ ብዥታ እንደሌለ እውን ነው፡፡ በተጨማሪም የሃይማኖታችንን ኢትዮጵያዊ ሚናና ሕልውና የሚመለከቱ አንኳር ገጽታዎች እንዳሉ ብናምንም በህዝብ ለተወከልንበት ጥያቄዎች ከመርህ አኳያ ምላሽ የተሰጠበትክስተትና ተግባራዊ ፍንጭም በመስተዋሉ፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ያልተመረጠ አመራርም ሲጥሰው የቆየውን መተዳደሪያ ደንቡን መርምሮ ራሱን ከሀላፊነት ለማግለል በመወሰኑ ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳው ጥያቄ ምላሽ የማግኘት ሂደት ላይ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ የስልጣን ሽግግሩ ህዝባዊነት በሌለውና የመጅሊሱ መዋቅር አካልና አጋር ለሆነው እንዲሁም መዋቅራዊአቅም ለሌለው የኡለማዎች ምክር ቤት መሰጠቱ አግባብ እንዳልሆነም ይሰማናል፡፡ ቢሆንም ሕዝበ ሙስሊሙ በቅርቡ ለሚደረገው የመጅሊስ ምርጫ ይሆኑኛል የሚላቸውን ተወካዮች ለመምረጥ ብርቱ ዝግጅት ከማድረግ በተጨማሪ ከኮሚቴው ጎን በመሆን አፈጻጸሙ ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ግልጽና ፍትሃዊ መሆኑን በንቃትእንዲከታተልም ጥሪ እናደርጋለን፡፡
በመላ ሀገሪቱ ያለው ህዝባዊ ጥያቄ ተመሳሳይ በመሆኑ መንግስት ካነሳነው ጥያቄ ጋር በተያያዘ ምክንያት ለእስር የተዳረጉ እንዲፈቱ፤ ማስፈራራቶችና የኃይል እርምጃዎች እንዲቆሙ ያደርግ ዘንድ አቤቱታችንን እናቀርባለን፡፡ ዴሞክራሲና እውነተኛ ሰላም ከማንም በላይለህዝበ ሙስሊሙ ብቸኛ የድል መስመሮች መሆናቸውን ድምጻችንን ለተጋሩ ሁሉ በድጋሚ እያሳሰብን ወደ ብጥብጥ ሊያስገቡየሚችሉ ድርጊቶች በመስጊዶችም ሆነ በማንኛውም ቦታ እንዳይከሰቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ በአላህ ስም እንጠይቃለን፡፡