በጎንደር ሃያ ሙስሊሞች መታሰራቸው ተገለፀ
ጎንደር ሃያ ሙስሊሞች መታሰራቸው ተገለፀ
አዲስ አበባ ሬዲዮ ቢላል ግንቦት 5/2004
በጎንደር ፎገራ ወረዳ አርማጮ ከተማ ለመስጂድ በተሰጠ ቦታ ላይ ሆቴል እንዲሰራ ያለአግባብ በመፈቀዱ የአካባቢው ሙስሊሞች ተቃውሞ በማሰማታቸው ሃያ ሰዎች ከመስጂድ ተወስደው መታሰራቸው ተገለፀ፡፡
የመስጂዱ ግንባታ እየተፋጠነ ባለበት ሁኔታ በኢንቨስትመንት ሽፋን ሆቴል በመስጂዱ ደጃፍ ላይ እንዲሰራ በመፍቀዱ የአካባቢው ሙስሊሞችና የመስጂዱ ኮሚቴዎች ለመንግስት አካላት አቤት ቢሉም እስከ አሁን ፈጣን ምላሽ አለማግኘታቸው ታውቋል፡፡
እንደ አካባቢው የሬዲዮ ቢላል ምንጭ መስጂዱ አዛን እንደማይባልበትና ሰላት እንዳይሰገድበት በከተማው የፀጥታ ዘርፍ አላፊ ታሽጓል ፡፡
የታሰሩት 20 ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ፖሊስ ጉዳዩን ለመመርመር የ5 ቀን ቀጠሮ ጠይቆ እንዲቆዩ ቢያደርግም ነገር ግን በትላንትናው ዕለት እንዲፈቱ በፖሊስ ትህዝ ተላልፎላቸው ነበር ሰዎቹ ግን ያለአግባብ እንደታሰሩና ፍትህ ሳያገኙ ከእስር ቤቱ እንደማይወጡ መግለፃቸውን ከምንጫችን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የመስጂዱ ኮሚቴዎች ጉዳያቸውን ለዞን እና ለክልል የመንግስት አካላት በማቅረብ ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
የአካባቢው ሙስሊም ህብረተሰብ በድርጊቱ እንደተቆጣና በሽማግሌዎችና በኮሚቴው አካላት አማካኝነት እንዲረጋጉ መደረጉንና ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ ከአካባቢው ምንጭ ለመረዳት ተችሏል፡፡